“ትግራይ ወጣቶች በየቀኑ የሚታፈሱባት ፍትሕ አልባ ክልል ሆናለች” -ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት
++++++++++++++++
#ጋዜጣ_ፕላስ │ ትግራይ ወጣቶች የሚሰደዱባት፣ በየቀኑ የሚታፈሱባትና በግዳጅ ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ የሚገቡባት ፍትሕ አልባ ክልል ሆናለች ሲሉ የስምረት ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ አባል ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት ገለጹ፡፡
ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት ለጋዜጣ ፕላስ እንደተናገሩት፤ የሕወሓት ቡድን በቅርቡ የትግራይን ሕዝብ መብት የሚጥስ አፋኝና ሕገ-ወጥ ሕግ አውጥቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ወጣቶች የሚሰደዱበት፣ በየቀኑ የሚታፈሱበትና ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ የሚገቡበት አሰጋጭና ፍትሕ አልባ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
በሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን ምክንያት የትግራይ ሕዝብ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ ይገኛል ያሉት ፕሮፌሰር ክንደያ፤ ወጣቶች በተለያየ መንገድ ወደ አዲስ አበባ፣ ወደ ሌሎች ክልሎችና ወደ ጎረቤት ሀገራት በስደት በመውጣታቸው የክልሉ ከተሞች ወጣት አልባ እየሆኑ መጣታቸውን አስረድተዋል፡፡
ቡድኑ ትግራይንና የትግራይን ሕዝብ እንደ መያዣ (ጋሻ) አድርጎ እየተጠቀመ መሆኑን በመጠቆም፤ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች በመጣሳቸው ምክንያት ሕዝቡ በከፍተኛ ደረጃ እየተሰቃየ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በትግራይ ክልል አመርቂና አስቻይ ሁኔታ ባለመኖሩ ምክንያት መሠረታዊ የሸቀጦች፣ የነዳጅና የሌሎች አቅርቦቶች እጥረት መከሰቱን የገለጹት ፕሮፌሰሩ፤ ይሁን እንጂ በፌዴራል መንግሥት የሚሰጡ መሠረታዊ የስልክ፣ የትራንስፖርትና ሌሎች አገልግሎቶች ቀጣይነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ሕገ-ወጥ የማዕድን ቁፋሮ፣ ሕገ-ወጥ የሰውና የመሣሪያ ዝውውር በየከተማው እንደሚፈጸም አብራርተው፤ በአሁኑ ወቅት ክልሉ በከፍተኛ አጠቃላይ ቀውስ ውስጥ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
የሕወሓት ቡድን የጊዜያዊ አስተዳደሩን በማፍረስ በኃይል ሥልጣን መቆጣጠሩንና ክልሉን ጨምድዶ በመያዝ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ምርጫ ሲካሄድ በትግራይ እንዳይካሄድ ማድረጉንም አብራርተዋል።
በማርቆስ በላይ
#ጋዜጣ_ፕላስ #ትግራይ #ስምረትፓርቲ #ሕወሓት #ሰብዓዊመብት #ኢትዮጵያ #GazettePlus #Tigray #Ethiopia
Post #46836
2.73K
- ❤ 4
- 👎 1