አነስተኛ ወርቅ አምራቾችን ወደ ኢንዱስትሪ መሪነት የማሸጋገር ሥራ እየተከናወነ ነው
+++++++++++++++++++
#ጋዜጣ_ፕላስ | በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አነስተኛ የወርቅ አምራቾችን ወደ ዘመናዊ የኢንዱስትሪ ባለቤትነት የሚያሸጋግር አሠራር በመዘርጋትና በቴክኖሎጂ በመደገፍ ወደ ኢንዱስትሪ መሪነት የማሸጋገር ሥራ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ማዕድን ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ናስር መሀመድ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በማዕድን ልማት ዘርፉ ለአካባቢው ነዋሪዎች ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ አነስተኛ አምራቾችን ወደ ዘመናዊ የኢንዱስትሪ ባለቤትነት የሚያሸጋግር ሥርዓት ተዘርግቷል።
አነስተኛ አምራቾችን በአምስት ሄክታር መሬት ላይ በማደራጀት ወደ ሥራ እንዲገቡ በተደረገው ጥረት እስካሁን ከ50 ሺህ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን የገለጹት አቶ ናስር፤ ይህ አደረጃጀት የአካባቢው ነዋሪዎች ያላቸውን የቆየ ልምድና እውቀት ከሕጋዊ አሠራር ጋር በማቀናጀት ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
አምራቾቹን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ወደ ተሻለ የኢንዱስትሪ ደረጃ የማሸጋገር ሥራ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን፤ ባለሀብቶች ከአነስተኛ አምራቾች ጋር በጋራ እንዲሠሩ ወይም ከ5 እስከ 50 ሄክታር መሬት ወስደው በኩባንያ ደረጃ እንዲሰማሩ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
ከወርቅ በተጨማሪ እንደ የድንጋይ ከሰል፣ እምነበረድ እና ብረት ያሉ 17 ዓይነት ማዕድናት ለክልሉ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ እንደ ሞተር እንዲያገለግሉ ጥናት እየተደረገባቸው እንደሚገኝም ምክትል ቢሮ ኃላፊው ጠቁመዋል።
በሳሙኤል ወንደሰን
#ጋዜጣ_ፕላስ #አነስተኛ_አምራቾች #ኢንዱስትሪ#ቤኒሻንጉል_ጉሙዝ #ማዕድን #ወርቅ #ኢትዮጵያ
Post #46271
1.77K

- ❤ 2