የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን አዲስ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋቱን አስታወቀ
+++++++++++++++++++
#ጋዜጣ_ፕላስ | በሀገሪቱ እየታየ ያለውን የነዳጅ እጥረትና ሕገወጥ ንግድ ለመፍታት በቴክኖሎጂ የታገዘ አዲስ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋቱን የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን አስታወቀ።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ደስታው መኳንንት (ዶ/ር) ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ በየዓመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በነዳጅ ስርቆት ወይም "መቀሸብ" ምክንያት በሕገወጥ መንገድ ይባክናል።
ችግሩ ከጅቡቲ ጀምሮ እስከ ማደያዎች ድረስ ባለው ሰንሰለት ውስጥ የሚፈጸም መሆኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አንድ የነዳጅ ቦቴ መንገድ ላይ በመቆም ብቻ በርካታ ሊትር ነዳጅ እንደሚሰረቅና በማደያዎችም "አየር በመሸጥ" እስከ 10 በመቶ የሚደርስ ስርቆት እንደሚፈጸም ተናግረዋል።
ይህንን ሕገወጥ ዝውውር ለመግታት መንግሥት የ40/20/40 የነዳጅ ሥርጭት ቀመር አዘጋጅቶ እየተገበረ ይገኛል።
ይህ አዲስ አሠራር የኩባንያዎችን የማደያ ብዛት፣ ነዳጅ የማከማቸት አቅምንና ሕዝቡን በቀጥታ የሚያገለግሉ የዲስፔንሰር ወይም የመቅጃ መሣሪያዎችን ቁጥር መሠረት በማድረግ ፍትሐዊና ቁጥጥር የሚደረግበት የነዳጅ ሥርጭት እንዲኖር ታስቦ የተቀረጸ መሆኑን አስረድተዋል።
በተጨማሪም በመንገድ ላይ የሚቀሸበውን ነዳጅ ለመቆጣጠር አላርም የሚያደርግ “ሴንሰር” በቦቴዎች ላይ እየተገጠመ መሆኑን ደስታው (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ በሕገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ መያዙን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በ352 ማደያዎችና በ256 ቦቴዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል።
በዮሐንስ መልካሙ
Post #46270
2.08K

- ❤ 2