“ህጋዊ የንግድ ስርዓትን የሚያቀጭጩ እና እንቅፋት የሚፈጥሩ ነገሮች በሙሉ ሊስተካከሉ ይገባል”
- አቶ ሙስጠፌ መሐመድ
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር
+++++++++++++++++++++++++
#ጋዜጣ_ፕላስ | ህጋዊ የንግድ ስርዓትን የሚያቀጭጩ እና እንቅፋት የሚፈጥሩ ነገሮች በሙሉ ሊስተካከሉ ይገባል ሲሉ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በጂግጂጋ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘውን “ጉምሩክ ስለኢትዮጵያ” የውይይት መድረክ ላይ የመክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ እንደገለጹት፤ ህገ-ወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድ ህጋዊ ነጋዴዎችን ከገበያ በማውጣት እና የሀገር ኢኮኖሚን በማቀጨጭ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል።
ኮንትሮባንድ የንግድ ስርዓቱን ከማዛባት ባሻገር የማህበረሰብ ጤና፣ ሰላም እና ደህንነት ላይ እክል የሚፈጥር የሀገር እክል ነው ብለዋል።
የኮንትሮባንድ መረብ ውስብስብ እና በርካታ ተዋናዮች ያሉበት በመሆኑ በፀጥታ አካላት ብቻ በሚደረግ ጥረት እልባት ሊያገኝ አይችልም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ይህንን የልማት ጠላት ለመከላከል እና ለማስወገድ ድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ህጋዊ ነጋዴዎች የንግድ ህግን አክብረው እና ለታክስ ህግ ተገዥ ሆነው በመስራት ለክልሉም ሆነ ለሀገሪቱ ገቢ እያስገኙ እንደሚገኙ አቶ ሙስጠፌ ገልጸዋል።
አክለውም፣ ክልሉ የሚሰራቸው የልማት ስራዎች ከግብር ከፋዩ በሚገኝ ገቢ የሚሰራ ነው፤ በዚህም ህጋዊ ነጋዴዎቻችን ሊኮሩ ይገባል ብለዋል።
ህጋዊ ነጋዴዎችን የንግድ ስራዎቻቸውን ለማስፋፋት ምቹ የንግድ ስነ-ምህዳር በመፍጠር እና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የክልሉ መንግስ እንደሚያበረታታቸውም አመልክተዋል።
በዮሐንስ መልካሙ (ጂግጂጋ)
Post #46185
3.02K





- ❤ 8