TGViewer
Gazette Plus / ጋዜጣ ፕላስ/ Gazette Plus / ጋዜጣ ፕላስ/ @ethpress · 24.8K subscribers
Post #46151 2.02K
53ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ውሳኔዎች

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 53ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

1. በቅድሚያ ምክር ቤቱ የተወያየው መደመር የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በአዋጅ ቁጥር 1294/2015 መሠረት ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ የሚቋቋም ሲሆን በዘርፉ ወጣቶችን ለማሰልጠንና ለሀገር ግንባታ ወሳኝ የሆኑ ምሁራንን ለማፍራት የሚሰራ ነው፡፡ ደንቡ የዩኒቨርሲቲውን ተግባርና ሃላፊነት በመደንገግ ተቋሙ ለሀገር ዕድገት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ የህግ ማዕቀፍ ሆኖ እንዲያገለግል ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው ለባለሃብቶች ካሳ ለመክፈል ግዴታ የሚገባበትን ሁኔታ ለመወሰን በቀረበ ደንብ ላይ ነው፡፡ ባለሀብቶች የሀገራችንን የኢኮኖሚ እድገት ሊያፋጥኑ በሚችሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች እና ቅድሚያ በሚሰጣቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንዲያስችል ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

3. ከዚያም ምክር ቤቱ የተወያየው በሶስት የፋይናንስ ድጋፍ ሰምምነቶች ላይ ነው፡፡ የመጀመሪው ለብሄራዊ ኤሌክትሪክ ኃይል ማስፋፊያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል ከኮሪያ ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ የስልሳ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሃያ ሶስት ሺ /60,223,000/ የአሜሪካን ዶላር ብድር ሲሆን ከወለድ ነጻ፣ ብድሩን በማስተዳደር ረገድ ለሚወጡ ወጪዎች 0.1% የአገልግሎት ክፍያ የሚከፈልበት እና የ15 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ40 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ነው፡፡

ሁለተኛው ለታዳሽ፣ የተቀናጀ፣ ዘላቂ ኃይል እና ዲጂታላይዜሽን ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል ከፈረንሳይ የልማት ኤጄንሲ የሰማንያ ሚሊዮን /80,000,000/ ዩሮ ብድር ሲሆን አነስተኛ ወለድ 1.2% የሚከፈልበት፣ ብድሩን በማስተዳደር ረገድ ለሚወጡ ወጪዎች 0.5% የአገልግሎት ክፍያ የሚከፈልበት እና የ7 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ20 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ነው፡፡

ሶስተኛው ለከተማ ልማታዊ ሴፍትኔትና ሥራ ፈጠራ የሚውል ከዓለም ዓቀፍ የልማት ማህበር የአንድ መቶ ሰማንያ አራት ሚሊዮን አንድ መቶ ሺ /184,100,000/ ኤስ ዲ አር ብድር ሲሆን ከወለድ ነጻ፣ ብድሩን በማስተዳደር ረገድ ለሚወጡ ወጪዎች እንዲሁም ጥቅም ላይ ላልዋለው ገንዘብ 1.25% የአገልግሎት ክፍያ የሚከፈልበትና የ6 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ30 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ሶስቱም የብድር ስምምነቶች ከአገራችን የብድር አስተዳደር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን በማረጋገጥ ረቂቅ አዋጆቹ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

4. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርአት ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ በሀገራችን የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዐትን ተግባራዊ ለማድረግ አዋጅ ቁጥር 372/1996 ወጥቶ በስራ ላይ የቆየ ቢሆንም ለአዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ ባለመውጣቱ በአፈጻጸም ሂደት ይስተዋሉ የነበሩ ክፍተቶችን ለማረም፣ ለአዋጁ አፈጻጸም አስቻይ የሆኑ ዝርዝር ጉዳዮችን ለመደንገግና አስፈላጊውን የቁጥጥር ሥርዐትና መዋቅራዊ አደረጃጀት ለመፍጠር እንዲያስችል ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

5. በተጨማሪም የወርቅ ማዕድን እና የብረት ማዕድን ምርት ፈቃድ ረቂቅ ስምምነቶች ላይ ምክር ቤቱ ተወያይቷል፡፡ ለምክር ቤቱ የቀረቡት ሁለት ረቂቅ ስምምነቶች የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ከማሳደግ፣ ለዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር፣ ለኢኮኖሚያችን አዎንታዊ ሚና ከመወጣት አንጻር ትልቅ ጠቀሜታ ያላቸውና ከአካባቢ ጥበቃና ከማህበረሰብ ተጠቃሚነት አንጻርም የመንግስትን የፖሊሲ አቅጣጫ የተከተሉ መሆናቸውን በማረጋገጥ የማዕድን ሚኒስቴር ስምምነቶቹን እንዲፈራረምና ወደ ስራ እንዲገቡ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ይሁንታ ሰጥቷል፡፡

6. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የቱሪዝም ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ነው፡፡ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ የነበረው የቱሪዝም ልማት ፖሊሲ በዘርፉ የተከሰቱ ለውጦችን ከማስተናገድ፣ መልካም አጋጣሚዎችና የመልማት አቅሞችን ከመጠቀም እና ለአገራዊ ዕድገት ሚናውን ከመወጣት አንጻር ክፍተቶች የነበሩበት ነው፡፡ ዘርፉን በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ከተቀመጠው የፖሊሲ አቅጣጫ ጋር አጣጥሞ በመምራት እና በማልማት ለአገራዊ ኢኮኖሚ እድገት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ማስቻል አስፈላጊ በመሆኑ ረቀቂ ፖሊሲው ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በፖሊሲው ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል በምክር ቤቱ ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

#PMOEthiopia
  • ❤ 3
More from @ethpress
  1. Oct 16, 2026የትግራይ ክልል የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ተመሠረተ ++++++++++++++++ #ጋዜጣ_ፕላስ- የፌዴ…
  2. Oct 13, 2026ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለተቋም አመራሮች ሹመት ሰጡ ++++++++++++++ #ጋዜጣ_ፕላስ- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (…
  3. Oct 13, 2026መረጃ ወደ ተግባራዊ መመሪያዎች ሲቀየር ሐብትን ይጠብቃል፣የተሻለ ውሳኔ ለመስጠት ያግዛል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) +++++++…
  4. Oct 13, 2026photo post
  5. Oct 12, 2026ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐ19ኛውን ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን ያስተላለፉት መልዕክት ++++++++++ ‎ ‎“ሠን…
  6. Oct 11, 2026የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መቀሌ የሚያደርገውን በረራ ጀመረ ++++++++++++ #ጋዜጣ_ፕላስ- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ…
Threads Profile ViewerView any public Threads profile without an account.Open ThreadLook →Writing with AI? Make it sound human.Metric37 rewrites AI drafts so they read naturally. Free AI detector, 1,500 words free.Try Metric37 →