ኢትዮጵያ የውጪና የገቢ ምርቶቿን ለማቀላጠፍ በ83 ቢሊዮን ብር ወጪ 16 መርከቦችን ልትገዛ ነው
++++++++++++++++
#ጋዜጣ_ፕላስ | ኢትዮጵያ አሁን ካሏት 10 መርከቦች በተጨማሪ በ83 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ 16 መርከቦችን ለመግዛት አቅዳ የስድስት መርከቦች ግዥ በሂደት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ የዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ዋና ክፍል ሥራ አስኪያጅ አቶ ስንታየሁ ኃይለማርያም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ ለወጪና ገቢ ምርቶች ከምትጠቀምባቸው 10 መርከቦች በተጨማሪ 16 መርከቦችን ለመግዛት አቅዳለች፡፡
መርከቦቹን በቀጣይ አምስት ዓመታት ለመግዛት የታቀደ ሲሆን፤ ለዚህም 83 ነጥብ1 ቢሊዮን ብር በጀት መያዙን ገልፀው መርከቦችን በግዥ የኢትዮጵያ የማድረግ ሥራ የተቋሙ የስትራቴጂክ ዕቅዶች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህም ስድስት መርከቦች ሕጋዊ የግዥ ሥርዓት በሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ የሚገኙ መርከቦች ጠቅላላ የመሸከም አቅም ከ25ሺ እስከ 28ሺ ሲሆን፤ የአዳዲሶቹ መጫን አቅም ከቀድሞቹ አንጻር ሲታይ ግዙፍና ከ50ሺ እስከ 63ሺ የመጫን አቅም ያላቸው ናቸው ብለዋል፡፡
የመርከቦቹ ግዥ በሀገሪቱ ስትራቴጂክ የሆኑ ግብዓቶችን ጨምሮ በርካታ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት እንዲሁም ወደ ውጭ የሚላከውን በቅልጥፍናና በወቅቱ በመላክ የሎጂስቲክስ እንቅስቃሴን ውጤታማነት ለማሳደግ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ተቋሙ በበጀት ዓመቱ በድርጅቱ መርከቦች፣ በስሎትና በኪራይ መርከቦች ብትን ዕቃን ጨምሮ 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቶን ገቢ ዕቃ ለማጓጓዝ ታቅዶ 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ቶን አጓጉዟል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት የመሆን ሕልሟን ለማሳካት ዘርፈ ብዙ ጥረት እያደረገች መሆኗን የገለጹት አቶ ስንታየሁ፤ ይህን ውጥን ታሳቢ ያደረጉ ተግባራትን ከግምት ውስጥ በማስገባት እየሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በክፍለዮሐንስ አንበርብር
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት#ጋዜጣፕላስ #መርከብ ግዥ#ገቢና ወጭ ምርቶች#ንግድ #ኢኮኖሚ#ኢትዮጵያ
Post #46883
3.18K
- ❤ 6
- 😁 1