"በሦስት ዓመታት ውስጥ ለማሳካት የታቀደውን ግብ ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ማሳካት ተችሏል”
- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
++++++++++++++++
#ጋዜጣ_ፕላስ በሦስት ዓመታት ውስጥ ለማሳካት የታቀደውን የ“5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮችን ግብ ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ማሳካት መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
እስከ ነሐሴ 2018 ዓ.ም ድረስ የሠልጣኞችን ቁጥር 7 ሚሊዮን ለማድረስ መታቀዱንም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ባሰፈሩት መልዕክት፣ “በሦስት ዓመታት ውስጥ ለማሳካት የታቀደውን ግብ ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ማሳካት ተችሏል። ለዚህም ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የ“5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች” ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ከተጀመረበት ጊዜ አንሥቶ በኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ፣ በመረጃ ትንተና፣ በአንድሮይድ ሶፍትዌር ልማትና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ ትምህርቶች 5,005,146 ሠልጣኞች ተመዝግበው ከ3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ሥልጠናውን አጠናቀዋል ብለዋል።
ይህ ስኬት የሕዝባችንን ቁርጠኝነት እና ወሰን የሌለው አቅም ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
በዲጂታሉ ዓለም በልኩ ለመዘጋጀት የጀመርነው ታሪካዊ ምዕራፍ፤ የጉዟችን ማብቂያ ሳይሆን፥ ብሔራዊ ርዕያችንን ይበልጥ የምናፋጥንበት መነሻ እንደሆነም ጠቁመዋል።
እስከ ነሐሴ 2018 ዓ.ም ድረስ የሠልጣኞችን ቁጥር 7 ሚሊዮን ለማድረስ የተሰነቀውን ግብ ለማሳካት፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የዚህ ብሔራዊ ተልዕኮ አካል እንዲሆን ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ለወጣት ተማሪዎቻችን፤ መጭው የክረምት ወቅት ትልቅ ዕድላችሁ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ጊዜያቸውን በዋዛ ከማሳለፍ ተቆጥበው በመመዝገብ እና በመማር ወደ ትምህርት ገበታቸው ሲመለሱ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያላቸው የዲጂታል መሪዎች እንዲሆኑ አሳስበዋል።
ሥልጠናዎቹ ሙሉ በሙሉ በነጻ የሚሰጡ ሲሆን፣ የምስክር ወረቀቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የምትገነቡት ነገ የሚጀምረው ዛሬ ነው!” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ለመመዝገብ እዚህ ይጫኑ- ethiocoders.et/
Post #46655
3.82K
- ❤ 10