በነጻ የንግድ ቀጣና ውስጥ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የገቢ ግብር ነጻ መብት ተፈቀደ
+++++++++++++++++
#ጋዜጣ_ፕላስ | በነጻ የንግድ ቀጣናዎች ውስጥ ተሰማርተው ግብዓቶችንና ምርቶችን ለገበያ የሚያቀርቡ ባለሀብቶች፣ በዘርፉ ያለባቸውን የፋይናንስ ጫና ለማቃለል ሲባል ከገቢ ግብር ነጻ እንዲሆኑ መወሰኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የአገሪቱ የኢንዱስትሪ ልማት በሚፈለገው መጠን እንዳያድግ እንቅፋት ከሆኑት መካከል የካፒታል እጥረት፣ የግብዓት አቅርቦት ችግርና የባለሙያ እጥረት በዋነኛነት የሚጠቀሱ መሆኑን ሚኒስቴሩ በመግለጫው አስታውቋል።
በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ደረጃ በደረጃ በማቃለል የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪ ልማትን ማሳደግ ይገባል ብሏል።
በዚህም መሠረት ግብዓቶችና ምርቶች በበቂ መጠን ለገበያ እንዲቀርቡ ለማድረግ፣ አስመጪዎች ምርቱን ለገበያ ከማቅረባቸው በፊት የሚከፍሉት ቀረጥና ታክስ ውስን በሆነው ካፒታላቸው ላይ የሚያሳድረውን ጫና ማቃለል አስፈላጊ ሆኖ እንደተገኘ አትቷል።
ለዚህም ሲባል አስመጪዎች ግብዓቶችንና ምርቶችን ቀረጥና ታክስ ሳይከፍሉ ወደ አገር አስገብተው ለምርቱ ገበያ ባገኙ ጊዜ ክፍያ የሚፈጽሙበት የነጻ የንግድ ቀጣና አሠራር የተዘረጋ ሲሆን፤ ይህም አስመጪዎች ምርቶችን ቀረጥና ታክስ ሳይከፍሉ አስገብተው ገበያ ሲያገኙ ብቻ እንዲከፍሉ የሚያስችል ነው።
እነዚህ ነጻ የንግድ ቀጣናዎች ባለሀብቶችን የበለጠ የሚስቡ እንዲሆኑ ለማድረግም፣ በነጻ የንግድ ቀጣናዎች ውስጥ ተሰማርተው ምርቶችን ለገበያ የሚያቀርቡ ባለሀብቶች ከገቢ ግብር ነጻ እንዲሆኑ ተፈቅዷል።
አሠራሩ የአስመጪዎችን ካፒታል በማንቀሳቀስ ረገድ ያለውን ጫና በእጅጉ የሚቀንስ ሲሆን፤ ሥርዓቱን የሚያስፈጽሙ ነጻ የንግድ ቀጣናዎችም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተቋቁመው ሥራ መጀመራቸው ተገልጿል።
Post #46441
2.46K

