ኢትዮጵያ የኃይል ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች
++++++++++++++++
#ጋዜጣ_ፕላስ | ኢትዮጵያ እኤአ በ2035 መቶ በመቶ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች።
በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ዳቢ ለጋዜጣ ፕላስ እንደገለጹት፤ ሀገሪቱ በ2035 መቶ በመቶ የኃይል ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች።
የኤሌክትሪክ ኃይልን ተደራሽነትን ለማሳካት ሁለት ዋና ዋና ስትራቴጂዎች ይተገበራሉ ያሉት መሪ ሥራ አስፈፃሚው፤ አንደኛው ከዋናው የኃይል ማሰራጫ መስመር ኤሌክትሪክን ማዳረስ ሲሆን፣ ሁለተኛው ከዋናው መስመር ርቀው የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን የሶላር (የፀሐይ) ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ተጠቃሚ ማድረግ ነው ብለዋል።
የሶላር ኃይል ተጠቃሚ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ በየአካባቢያቸው የመሰረተ ልማት ዕድገት እየተስፋፋ ሲመጣ ዘላቂና አስተማማኝ ወደ ሆነው ዋናው መስመር የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንደሚሸጋገሩም ተናግረዋል።
በሚቀጥሉት 10 ዓመታት የኃይ አቅርቦት ተደራሽነት ለማረጋገጥ 18 ቢሊዮን ዶላር ፋይናንስ እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ መስፍን፤ አስፈላጊውን በጀት ከመንግሥት፣ ከግሉ ዘርፍና ከአለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የማሰባሰብ ሥራውን ለማከናወን አቅጣጫ መቀመጡን ጠቁመዋል።
ባለፉት ዓመታት የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋፋት በተከናወኑ ተግባራት የሀገሪቱን አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ሽፋን 65 በመቶ ማድረስ መቻሉንም መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ዳቢ ገልጸዋል።
በክብረአብ በላቸው
#ጋዜጣ_ፕላስ #ኢትዮጵያ #የኤሌክትሪክ_ሽፋን #መሰረተ_ልማት #ታዳሽ_ኃይል
Post #46736
2.4K

- ❤ 1