"የትምህርት ስርዓቱ ከአቋራጭ መንገድ ተላቆ በብቃት ላይ እንዲመሰረት እየተሰራ ነው"
- ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
++++++++++++++
#ጋዜጣ-ፕላስ | በትምህርት ዘርፉ በአቋራጭ ዲግሪ የማግኘት የተሳሳተ አመለካከትን በመለወጥ በትክክለኛ እውቀትና ጥረት ላይ የተመሰረተ ትውልድ ለመገንባት ቁርጠኛ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስታወቁ።
የ100 ቀናት የመንግስት የስራ አፈጻጸም ግምገማን በተመለከተ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ ቀደም ባሉት ዓመታት የትምህርት ጥራትና የዘርፉ ታማኝነት በእጅጉ ተጎድቶ ቆይቷል።
ትምህርት በአቋራጭ የሚገኝ ተደርጎ መወሰዱ ያልተማሩ ሰዎችን በወረቀት ብቻ ተምረዋል ለማለት የሚያስገድድ መጥፎ ውጤት አስከትሎ እንደነበር አስታውሰው፤ ይህንን ሁኔታ ለመቀየር የትምህርት ቤቶችና የዩኒቨርሲቲዎች ፈተና ጥብቅ እንዲሆን በማድረግ ተማሪዎች ውጤት ማግኘት የሚችሉት ሰርተውና አጥንተው ብቻ መሆኑን የሚያረጋግጥ ስርአት መዘርጋቱን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች ዲግሪ ሲሰጡ ግለሰቡ በዘርፉ በቂ እውቀት እንዳለው ማረጋገጫ መሆን እንዳለበት የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ የውሸት ዲግሪ ማተም የህብረተሰቡን መሰረት ያናጋል ብለዋል።
በፈተናዎች ላይ የተደረገው ጥብቅ ቁጥጥር መጀመሪያ ላይ ተግዳሮቶች ቢገጥሙትም አሁን ላይ ተማሪዎች ወደ ጥናት ቤተሰቦች ደግሞ ልጆቻቸውን ወደ ማበረታታት መመለሳቸውን ጠቁመዋል።
የተማሪዎችን ተሳትፎና የትምህርት አቀባበልን ለማሳደግ መንግስት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አንስተው፤ በትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም የሚደርግላቸው ተማሪዎች ቁጥር ወደ 8 ሚሊዮን ማደጉንም ገልጸዋል።
ከለውጡ በፊት 4 ሺህ አካባቢ የነበረው የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ቁጥር ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ወደ 34 ሺህ ማደጉን አስታውቀዋል።
በዚህ ዓመትም ምንም አይነት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት በሌለባቸው 626 ወረዳዎች ውስጥ 1 ሺህ 452 አዳዲስ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት አዲስ ኢኒሼቲቭ ተቀርጾ ወደ ስራ መገባቱን አመላክተዋል።
ይህም ከተማና ገጠር ሳይለይ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ልጅ እኩል የትምህርት ዕድልን ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
Post #46493
2.02K
- 👍 3
- ❤ 1