ኢሕአፓ በእስር ላይ የሚገኙት አባላቱ የዋስትና ውሳኔ ይፈጸም ወይም ይግባኙ በአፋጣኝ ይታይ ሲል ጠየቀ።
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ(ኢሕአፓ) በእስር ላይ ያሉ የፓርቲው አባላት በተመለከተ ቀደም ሲል የተሰጠው የዋስትና ውሳኔ እንዲፈጸም ወይም በውሳኔው ላይ የቀረበው ይግባኝ በአፋጣኝ ተመርምሮ ተገቢው የፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲሰጥ ጠይቋል።
ፓርቲው ባወጣው መግለጫ፤ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ይስሐቅ ወልዳይ፣ አባሉ አበበ ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተጠሪው ደረጄ ደለና እንዲሁም ጠበቃ አበራ ንጉስ አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ ገልጿል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ከተደጋጋሚ የምርመራ ቀጠሮዎች በኋላ ነሐሴ 29 ቀን 2018 ዓ.ም. በ50 ሺህ ብር ዋስትና እንዲለቀቁ የፍርድ ቤት ውሳኔ ተሰጥቶ እንደነበር አስታው፤ የፌዴራል ፖሊስ በዋስትና ውሳኔው ላይ ይግባኝ በማቅረቡ ጉዳዩ በይግባኝ ሂደት ላይ ይገኛል፤ በዚህም ተጠርጣሪዎቹ እስካሁን ከእስር እንዳልተለቀቁ አመልክቷል።
ኢሕአፓ የዋስትና ጉዳዩ በአፋጣኝ እንዲታይ፣ ቀደም ሲል የተሰጠው የዋስትና ውሳኔ እንዲፈጸም ወይም ይግባኙ በፍጥነት ተመርምሮ ተገቢው የፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲሰጥ ጠይቋል።
በተጨማሪም የተጠርጣሪዎቹ የግል ነፃነትና የፍትሕ መብት እንዲከበር፣ የፍርድ ሂደቱም በተደጋጋሚ ቀጠሮዎች እንዳይጓተት እና የፍርድ ቤቶች ነፃነትና ገለልተኛነት እንዲጠበቅ አሳስቧል።
ፓርቲው የአባላቱ ጉዳይ በፍጥነት፣ በግልጽነትና በሕግ መሠረት እንዲታይ በመግለጫው አሳስቧል።
#Ethiopia #ethiopia_today #ethiopian_news #addis_ababa #amharic_news #borkena_news #ኢትዮጵያ #አዲስ_አበባ #ኢህአፓ #ትብብር #የፖለቲካ_እስረኞች #አማርኛ_ዜና #ዜና #ቦርከና_ዜና
Post #7259
822


- 👍 3
- 😁 1