AB PHOTOGRAPHY & GRAPHIC DESIGN
ትውልዳችን፡-
1) መዳረሻውን ያላየ ነው
ከትውልዳችን አብዛኛውን የመጨረሻ ግቡ ገንዘብ ማግኘት ወይም ዝነኛ መሆን ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች የተጠሉና የማያስፈልጉም ባይሆኑም ራዕይ ግን አይደሉም፡፡ ትውልዳችን የተሻለ ኑሮ እፈልጋለሁ ይላል ፣ ለእርሱ የተሻለው ቤትና መኪና ነው፡፡ ሰውን ለሚያህል ትልቅ ፍጡር ግን እነዚህ ቁሳቁሶች ግብ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ መንገዳችን ላይ ከምናገኛቸው በረከቶች ውስጥ ይመደባሉ። ግባችን ግን ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ሰው ከበሬ ለተሻለ ነገር መኖር አለበት፡፡ በሬ ቀኑን በሙሉ ላቡን ጠብ አድርጎ ይሰራል ፤ እኛም እንሰራለን ፤ በሬ ከስራ መልስ ላም አለችው እኛም ትዳር አለን፡፡ በሬ ጥጆች አሉት እኛም ልጆች አሉን፡፡ ከዚህ ያለፈ ነገር ከሌለን እየኖርን ያለነው እንደ በሬ ነው ለማለት ነው፡፡ ስለዚህ ደስተኛ ባንሆን ምን ይደንቃል፡፡
ወደላቀው የኑሮ ደረጃ ፣ እግዚአብሔር ወዳየልን ከፍታ መድረስ አለብን፡፡ እርሱም በራዕይ መገለጥ ነው፡፡ ከሕይወት ጥያቄዎች አንዱ "ወዴት ነው የምሄደው?" የሚል ነው፡፡ ሰው መዳረሻውን ካላወቀ በኑሮው ድፍረት አይሰማውም፡፡
ትውልዳችን ላይ በአብዛኛው የምናየው ለዛሬ መሙላት ብቻ መኖር ፣ ለራስ ብቻም ማሰብ ፣ ሁሉንም ሰው የጥቅሙ ገባር አድርጎ መፈለግን ነው፡፡ ለወገኔ የሚል ስሜቱ እየተሟጠጠ ነው፡፡ ለዚህ ትልቁ ችግር በእግዚአብሔር የለሽ አስተሳሰብ መበከሉ ነው፡፡ ፈጣሪ የለሽ ሥርዓት ከአደባባይ ቢወድቅም ከሰው ልብ ግን አልወደቀም፡፡
በየትምህርት ቤቱ ይሰጡ የነበሩ የግብረ ገብ ትምህርቶች በአዋጅ መከልከላቸው ከዚያ በኋላ ያተረፍነው ትውልድ ብኩን ትውልድ ነው፡፡ ትዕግስት የጎደለው ፣ ራዕይ አልባ ፣ መረን ትውልድ ለማፍራት ተገደናል፡፡
2) ውለታቢስነት ተቆራኝቶታል
አይሁዶች:- "ተቀብሎ የማያመሰግን ከቀማኛ ይቆጠራል" ይላሉ አብዛኛው ትውልዳችን ከእግዚአብሔር ፣ ከቤተሰቡ ፣ ከሀገሩ ከመምህራኖቹ ተቀብሎ ፣ እንደ ጩልፊት ነጥቆ የሚሮጥ እንጂ ለምስጋና የሚመለስ አይደለም፡፡ ውለታቢስነት ተቆራኝቶታል፡፡
ሰዎች እንዲያደርጉለት እንጂ እርሱ ለማንም በጎ ለማድረግ አይሻም፡፡ የሚያስፈልገውን ነገር ያደረጉለትን ሰዎች እንደሞኝ ያያል እንጂ ፍቅራቸውን እንኳን መረዳት አይሆንለትም፡፡ ሁሉንም ሰው ወላጆቹን እንኳን ሳይቀር ለጥቅሙ መሟላት ያፈላልጋል፡፡ ጥቅሙን የሚያሟላለት ከመሰለው ምንም ከመሆን ፣ ከመጣመር ወደኋላ አይልም፡፡
ፍላጎቱ ጣዖት ሆኖበታል፡፡ ጥቅሙን የሚያሟሉለት ከሆነ የራሱን ሰዎች እንኳን ይጠላል፡፡ አንዳንዴም ይተናኮላል፡፡ ያስተማረችውን አገሩን ለማገልገል አይፈልግም፡፡
ሁሉም ነገር ተመቻችቶለት መቀመጥ እንጂ ተግዳሮትን በፍጹም አይፈልግም፡፡ ቀለል ያለውን በመምረጥ ሲጓዝ ቀለል ያለ መስሎ የሚገኝለት ሱስና ሀጢያት ሆኖ ይቀዘፋል፡፡
ትውልዳችን አብዛኛው ወላጆቹን ለመርዳት ፣ ለማመስገን እንኳን ፈቃደኛ አይደለም፡፡ እራሴን መቻሌ የመርዳት ያህል ነው ብሎ በአፉ ይናገራል፡፡ ወላጆቹ የልጆቻቸውን ስጦታ ሲያጡ "ራሱን መቻሉ ጥሩ ነው" ብለው የሚጽናኑበትን ቃል እርሱ መኩሪያ አድርጎ መጠቀሙ ያሳፍራል፡፡
ገንዘብ ይበትናል እንጂ ጥሩ እርሻ ላይ አይዘራውም፡፡ ለአዝማሪና ለዝሙት ይበትነዋል፡፡ ደስታው ለራሱ ፣ መከራውን ለወላጆቹ መመደቡ በጣም አሳዛኝ አድርጎታል፡፡
ትውልዳችን ያስተማሩትን መምህራኑን የማያከብር ፣ ለራሱ መስፍን ሆኖ ንጉስ አልባ የሆነ ትውልድ ነው፡፡ የሌሎች ውለታ መመለስ መቻል የሰውነት ክብር ነው፡፡ ውለታን ማሰብ እንኳ አለመፈለግ ግን ከሰውነት ተራ የሚያወጣ ነው፡፡ በፈረንጆች አገር የእናቶች ቀን የመምህራን ቀን እያሉ ፍቅርን በዓል ያደረጉት በትውልዱ ውለታ ቢስነት ነው፡፡
3) ራሱን የማያከብር ነው
ራስን መሆን ለአእምር ጤንነት ፣ ለኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ነው፡፡ ራሱን ያልሆነም እራሱንም ያጣል፡፡ ሌሎች ሊያከብሩት የሚችሉት መጀመሪያ እራሳችንን ስናከብር ነው፡፡ ራቁታችንን በራሳችን ሸማ ብንሸፍነውም እንሰወራለን ፤ በሌሎችም ልብስ ግን ሐፍረታችን አይሸፈንም፡፡
ትውልዳችንን ስናየው ገና በአእምሮ ቅኝ ግዛት የተያዘ ፣ እራሱን የማያከብር ፣ ከራሱ መልካም የሌሎችን ክፉ እንደ መልካም የተቀበለ ትውልድ ነው፡፡ ስለዚህ የረጋ ማንነት የለውም፡፡ ሕይወቱን የሚመራው ዘመናዊነት እንጂ ቋሚ እውነት አይደለም ፤ በሳምንቱን ምርጥ ፊልም ሳምንቱን ይመራዋል፡፡ መረጃዎቹን ለመስማት ሳይሆን ለመሆን ስለሚፈልግ በብዙ ጠፍቷል፡፡ ስለ ሌሎች ሲያወራ ስለ ኳስ ተጫዋቾች ደሞዝ ሲጨቃጨቅ ይውላል፡፡ አንድ አባባል አለ፡-
"ትልልቅ ጭንቅላቶች ስለ አሳብ ያወራሉ ፣ መካከለኛ ጭንቅላቶቹ ስለ ሁኔታ ያወራሉ ፣ ትንንሽ ጭንቅላቶች ሁሌም ስለ ሰው ያወራሉ"
እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰው የሰጠው ማንነት አለ፡፡ ያ ማንነት የተለያየ ቢሆንም እግዚአብሔር ከሰማይ ወደምድር ሲመለከት የተለያየ ቀለምን የሚያሳይ ኪነ ጥበብ ነው፡፡ ራሳችንን ስንሆን እግዚአብሔር ሊያይ የፈለገውን ሥዕል እናሟላለን፡፡ ከሌሎች መማር አስፈላጊ ቢሆንም የምንቆምበት መሠረት ግን ያስፈልገናል፡፡ መሠረቱን ለቆ ዕቃ ላውርድ የሚል ዕቃውን ይዞ እንደሚወድቅ እንዲሁ ማንነቱን ጥሎ ከሌሎቹ ልማር የሚል ትምህርቱ ለመቆም አይረዳውም፡፡
ትውልዳችን እንደሌሎቹ መናገር ፣ እንደሌሎቹ መራመድ ፣ እንደሌልቹ መልበስ የሚያረካው የራሱ ነገር በጣም የሚያሳፍረው ነው፡፡
የገንዘብ ባሪያ ሆኖም ገንዘብን ለማግኘት ምንም መሆን የማይቆጨው ፣ ሰውነቱን አርክሶ ገንዘብ መሰብሰብ የሚያስደስተው ነው፡፡ ብዙ ወጣት ሴቶች ስናይ ገንዘብ ካዩ ምንም ዓይነት ክፉ ግብዣን እምቢ የማይሉ ፣ በባዕድ አገር ጭምር አገራቸውን የሚሰድቡ ክብር የለሽ ሆነዋል። ትውልዱን ራሱን አለማክበር ብቻ ሳይሆን ታላላቆቹን በመናቅ ትልቅ የሚሆን ይመስለዋል፡፡
Post #2040
837